ከመጠን በላይ መወፈር ማለት በሰውነት የተጠራቀመው የስብ መጠን አደገኛ የጤና ስጋት ደረጃ ሲደርስ ነው።
በሰውነት የተጠራቀመ ከፍተኛ የቅባት መጠን ለስኳር በሽታ ፣ለልብ ድካም ፣ለደም ግፊት ፣ለመገጣጠሚያ ህመም ፣ ለከፍተኛ ማንኮራፋት በሽታ ፣ ለስትሮክ ፣ለሀሞት ጠጠርና ለኮሌስትሮል በሽታዎች ይዳርጋል።
የቦዲ ማስ ኢንዴክስ /BMI ከ25 በላይ ከሆነ ከመጠን በላይ ወፍረዋል። ከ30 በላይ ከሆኑ ደሞ በአስጊ ደረጃ ወፍረዋል ። የአንድ ሰው BMI የሚሰላው ክብደቱን በኪሎ ለቁመቱ ልክ በሜትር ሁለቴ በማካፈል ነው። ለምሳሌ ክብደት 65 ኪሎ ቢሆንና ቁመት 1ሜትር ከ70 ሴ ሜ ቢሆን። 65ሲካፈል 1.7 አሁንም ሲካፈል 1.7=22.49 ይሆናል።ከ18.5 እስከ 24.9 ከሆነ በጣም ጥሩ ነው።
መልካሙ ነገር ክብደት ቀስ ብለው ትንሽ በትንሽ በመቀነስ የጤና ሁኔታን በከፍተኛ ማሻሻል ይቻላል። የክብደትን ከ5% እስከ 10 በመቶ በ6 ወር ውስጥ መቀነስ ተመራጭ ዘዴ ነው። የስነ ምግብ ባለሙያ(nutritionist) እና የስፖርት ባለሙያ እገዛ ቢያገኙ ሂደቱን ያቀልሎታል።
የክብደት መቀነሻ መድሀኒቶች
ትንሽ ትንሽ መብላትና ብዙ መስራት /መንቀሳቀስ የጎንዮሽ ጉዳት የሌላቸው እና ተጨማሪ ወጪ የማይጠይቁ ዘላቂ የውፍረት መቀነሻ ዘዴዎች ናቸው። ለአንዳንድ ሰዎች ተጨማሪ መድኃኒት ቢያስፈልጋቸውም አመጋገብና እንቅስቃሴ ማድረግ አስፈላጊ ነው።
የክብደት መጠን በጣም ከፍ ካለ (BMI>30) ወይ ደሞ ከ27 በላይ ሆኖ ሰኳር ወይም ግፊት ካለቦት መድኃኒት ሊታዘዝሎት ይችላል። እኛም ሀገር እንደ ኦርሊስታት(orlistat) ያሉ መድሀኒቶች በገበያ ላይ የሚገኙ ሲሆን እነዚህን መድሀኒቶች ከመውሰዶ በፊት ሐኪሞን ያማክሩ። በተለይ ነፍሰ ጡር፣ አጥቢና ለማርገዝ ካሰቡ እነዚህ መድሀኒቶችን መውሰድ አይመከርም።
ክብደት ለመቀነስ የሚረዱ ዘዴዎች
1.የምግብ መጠን መቀነስ (ትንሽ ትንሽ መብላት)
2.የታሸጉ ምግቦችን ሲጠቀሙ የካሎሪ መጠናቸውን ማየትና መጠንቀቅ
3.ብዙ ውሃ በመጠጣት የረሀብ ስሜትንና መመገብን መቀነስ
4.አትክልትና ፍራፍሬ ማዘውተር
5.ስኳር መቀነስ(በሻይ ፣በቡና፣ በለስላሳ መጠጥ፣ በኬክ፣ በኩኪስ )
6.ጥሩ ቅባት ያላቸውን ምግቦች መመገብ (አሳ፣ለውዝ፣የዌራ ዘይት)
7.ትንሽ ትንሽ በዙ ጊዜ መመገብ (እንዳይርብና ብዙ እንዳይበሉ ያደርጋል )
8.የእግር ጉዞ ማብዛት
9.ሳይክል መንዳት ፣ ዋና መዋኘት
10.ስፖርት መስራት