በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት ከፍተኛ ማቅለሽለሽና ትውከት ምንድን ነው?
ይህ ብዙውን ጊዜ ከእርግዝና ጋር የሚከሰት ሲሆን ጠዋት ጠዋት ብቻ፣ ቀትር ላይ ፣ ከሰአት በኋላ ወይም ቀኑን ሙሉ ያለማቋረጥ በመከሰት እናቲቱን ለከፍተኛ ዉሃ ጥም፣ ለክብደት መቀነስ እና ለተለያዩ የሚነራሎች መዛባት ሊዳርግ የሚችል ሁኔታ ነው። በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት ማቅለሽለሽና ትውከት አብዛኛውን ጊዜ በመጀመሪያዎቹ 8 እስከ 16 የእርግዝና ሳምንታት ውስጥ እየቀነሰ ሄዶ ይቆማል።
ምክንያቱ ምንድነዉ?
ምክንያቱ በዉል ይሄ ነዉ የሚባል ባይሆንም እንደ መላምትነት ከሚቀመጡት መካከል፡-
● በእርግዝና ጊዜ በ እንግዴ ልጅ የሚመረተዉ ሆርሞን (human chorionic gonadotropin (HCG))
● የስነ ልቦና ጫና
● በቂ የሆነ ካርቦ ሃይድሬት ምግብ ያለ መዉሰድ ይካተቱበታል።
✔️በእርግዝና ጊዜ የሚከስት የማቅለሽለሽና ትውከት ስሜት እንዲቀንስልኝ ምን ማድረግ አለብኝ?
የሚከተሉት በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት ማቅለሽለሽና ትውከት እንዲቀንስ ይረዳሉ
● ቅባት የበዛባቸውና ቶሎ የማይፈጬ ምግቦችን በብዛት በአንዴ ያለመመገብ
● ከተመገቡ በኋላ የሚረብሹትን ምግቦች እያዩ መቀነስ
● በቀን ውስጥ አነስ አነስ ያሉ ምግቦችን ብዙ ጊዜ መዉሰድ
● መጠነኛ የሆነ የ ቀረፋ ሻይ መጠቀም
● በሃኪም የሚታዘዙ የትውከት መድሃኒቶችን በመውሰድ በቂ እረፍት ማድረግ
● የሚያስጨንቅ ወይም የሚያሳስብ ጉዳይ ካለ ለሌላዉ ቤተሰብ አካል በማካፈል
ከጭንቀት ማረፍ
✔️ሃኪም ማየት ያስፈልገኛል?
ከማቅለሽለሹ ጋራ አብሮ ማስታወክ ካለ፣ በዚህም ምክኒያት ምግብ የማይረጋ ከሆነና የክብደት መቀነስ ካስከተለ ሃኪም ቤት ሄዶ ህክምና ማድረግ ያስፈልጋል።
በተጨማሪም ከስር የተጠቀሱት ምልክቶች ከታዩ ሃኪም ማማከር አስፈላጊ ነው
● ደም የቀላቀለ ትውከት
● ከባድ የሆድ ቁርጠት ወይም ህመም
● የሰውነት የፈሳሽ መጠን መቀነስ ምልክቶች ለምሳሌ የሽንት መጠን መቀነስ ፣ የሽንት መቅላት ፣ ከተቀመጡበት ሲነሱ መንገዳገድ
እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ በደም ስር የሚሰጥ ፈሳሽ እና የትውከት ማስታገሻ መድኃኒት መውሰድ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል ።