ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ከአንድ ነጭ ተማሪያቸው ጋር በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ ሆነው ህመምተኞችን እየጎበኙ ነው።
አንድ በአንድ ህመምተኞቹን እያዳረሱ ፣ አንድ በእድሜያቸው ገፋ ያሉ አዛውንት ጋር ደረሱ።
.
አዛውንቱ ነጭ–አምላኩ ነበሩና " ነጩ ዶክተር ካላከመኝ" ብለው ድርቅ አሉ። እንግዲህ ወጣቱ ነጭ ፕሮፌሰር አስራትን ፣ በትምህርት ደረጃ ፣ በስራ ልምድ ፣ በግል ተሰጥኦ ይወዳደራል ተብሎ አይታሰብም ። ከእርሳቸው ሰፊ ልምድ ፣ ስር ሆኖ ሊማር በፈቃደኝነት የመጣ ነው።
.
አዛውንቱ ግን በሀሳባቸው ፀኑ። ስለዚህ ፕሮፌሰር አሥራት መላ ዘየዱ። እርሳቸው ለነጩ ተማሪ እንደ ረዳት ሆነው አዛውንቱን ሊመረምሩ። በዚህ መሰረት ነጩ ተማሪ የፕሮፌሰር አሥራትን መመሪያ እየተከተለ አዛውንቱን መረመረ። በሽታቸውም ታወቀ።
.
ፕሮፌሰር አሥራት የፈውስ መድሃኒቱን ማዘዣው ላይ ፅፈው ለነጩ ተማሪ አስረከቡ። ተማሪው ደግሞ ለአዛውንቱ።
.
አዛውንቱ ፣ መልአክ የመሰለ ነጭ ሰው ስላከማቸው በጣም እየተደሰቱ፣ ገና መድሃኒቱን ሳይወስዱ የመሻል ስሜት እየተሰማቸው ፣ ሆስፒታሉን ለቀው ወጡ።
.
ከጥቂት ሳምንታት በኋላ፣ ፕሮፌሰር አሥራት ያንን አዛውንት ከመንገድ ያገኟቸዋል። የተለመደ ጥያቄያቸውንም ይሰነዝራሉ ፦ "እንዴት ኖት አሁን? ጨርሶ ተሻሎት?"
.
አዛውንቱ ሲመልሱ ፦ "አሁን ፍፁም ጤነኛ ነኝ። ጭራሽ አሞኝ አያውቅም። ያ የተባረከ ፈረንጅ በሙሉ ነው የፈወሰኝ"
.
ፕሮፌሰር አሥራት በአዛውንቱ የጤንነት ሁኔታ ተደስተው፣ አሁን እውነቱን ብነግራቸው ችግር የለውም ብለው አሰቡና፦ "ይኸውሎት አባቴ፣ ፈረንጁ የኔ ተማሪ ነበር ፣ ከኔ ሊማር ነው የመጣው። ያከምዎት ፣ ህመምዎን ያገኘሎት ፣ መድሐኒት ያዘዘሎት እሱ አይደለም፣ እኔ ነኝ" ቢሉ፣
.
አዛውንቱ መልሰው፦ "ለዚያ ነዋ ህመሙ እየደጋገመ የሚነሳብኝ!"
.
ምንጭ: Tewodros Shewangizaw, Book For All