በሩን ቆልፌዋለሁ ወይስ አልቆለፍኩትም? ስቶቩን አጥፍቼዋለሁ ወይስ አላጠፋሁትም? የሚል ሀሳብ መጥቶባችሁ ሄዳችሁ ቼክ አድርጋችሁ የምታውቁ ከሆነ የኦሲዲ (OCD) ምልክት በትንሹም ቢሆን አጋጥሟችሁ ያውቃል።
ኦሲዲ በአጭሩ ሲገለፅ ጥርጣሬ የሚፈጥር የሚነዘንዝ ሀሳብና ያንን ሀሳብ ተከትሎ የሚመጣውን ጭንቀት ለማርገብ የሚደረግ ተደጋጋሚ ድርጊት ነው። አንዳንድ ኦሲዲ ያለባቸው ሰዎች "የሚለውን ካላደረግኩ የሚያጨናንቅ ጉልቤ አእምሮ ውስጥ ያለ ይመስለኛል።" ይላሉ።
.
አንድ ኦሲዲ ያለባት ሴት አእምሮ ውስጥ፦
.
ወንበር ስትነካ እጇ የቆሸሸ ይመስላትና አእምሮዋ "ታጠቢ፣ ታጠቢ" እያለ ይነዘንዛታል። ንዝንዙ (ይህን ቃል ስፅፍ በወፍ ቋንቋ እያወራሁ መስሎኝ ነበር?) ሲበዛባት ለመታጠብ ትነሳለች። አእምሮዋ "የውሀ መክፈቻውም ቆሻሻ እኮ ነው።" ይላታል። መጀመሪያ መክፈቻውን ለአምስት ደቂቃ ታጥባለች።
.
አእምሮዋ ይቀጥልና "ሳሙናውም እኮ ቆሻሻ ነው።" ይላታል። ሳሙናውን ለአምስት ደቂቃ ሙልጭ አድርጋ ታጥባለች። ከዛ መታጠብ ትጀምራለች። አእምሮዋ "እዛ ጋር ይቀራል፣ እዚ ጋር ይቀራል።" እያለ መታጠብ ያለባትን ቦታ ይጠቁማታል። እሷም ትታዘዛለች። ታጥባ ልትጨርስ ስትል "የውሀ ፍንጣቂ ነክቶሻል፤ ታጠቢ" ይላታል። እንደገና ትታጠባለች....
.
ቤተሰቦቿና የስራ ባልደረቦቿ "እሷ መታጠቢያ ቤት ከገባች አትወጣም።" ይሏታል።
.
በታክሲ ስትሄድ አጠገቧ የሚቀመጠው ሰው ባይነካት ደስ ይላታል። የታክሲ ረዳቱ መልስ ሲሰጣት የእጁን ንፅህና ትመለከታለች። ከመቼ ወርዳ እስከምትታጠብ ይጨንቃታል። የበር እጀታ ባትነካ ትመርጣለች....ጭንቀቱን አስቡት። የሚጠፋውን ጊዜ አስቡት። ማህበራዊ ህይወት ላይ የሚያሳድረውን ተፅእኖ አስቡት።
.
ኦሲዲ የሚታከም የአእምሮ ህመም ነው።