የትምህርት ሚኒስቴር ከጤና ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የኮቪድ-19 ስርጭትን ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ትምህርትን ለማስጀመር የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡
የቅድመ ዝግጅቱ አካል የሆነው የአሰልጣኞች ስልጠና ከጤና ሚኒስቴር፣ ከትምህርት ሚኒስትቴር እንዲሁም ከሁሉም ክልሎች የትምህርት እና የጤና ቢሮ አመራርና ባለሙያዎች የአሰልጣኞች ስልጠና ዛሬ በአዳማ ከተማ መሰጠት ተጀምሯል፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻው አባይነህ ስልጠናውን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለፁት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የዓለም፣ የአፍሪካ ብሎም የሀገራችን ኢትዮጵያ ከፍተኛ ስጋት ነው ነገር ግን ትምህርት መጀመር ደግሞ አማራጭ የሌለው ጉዳይ በመሆኑ የኮቪድ-19 ስርጭትን ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ሁሉም ባለ ድርሻ አካል የተማሪ ወላጆችን ጮምሮ ኃላፊነታችንን መወጣት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ አክለውም ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ሲልኩ የኮቪድ-19 መከላከያ ዘዴዎችን ማለትም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በአግባቡ በ መጠቀም እንዲችሉ በማሳየት፣ እጃቸውን በውሃና በሳሙና በአግባቡ መታጠብ እንዲችሉ ወይም ሳኒታይዘር እንዲጠቀሙ እና በተቻለ መጠን እርቀታቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው ማስገንዘብ ከወላጅ(አሳዳጊ) የሚጠበቅ ሲሆን መምህራን፣የወላጅ መምህራን ማህበር፣ በትምህርት ቤቱ አቅራቢያ የሚገኙ ጤና ተቋማትና ባለሙያዎች እንዲሁም የትምህርትና የጤናው ዘርፍ አመራሮች በመቀናጀት ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ የመማር ማስተማሩ ስራ በስኬት እንዲጀመር ሁሉም መረባረብ እደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ስልጠናውም ለቀጣይ አምስት ቀናት ይቆያል፡፡