የፖሊዮ ክትባት ዘመቻን አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስቴር እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በሃገራችን የተለያዩ ክፍሎች የሕብረተሰብ ጤና ስጋቶች ላይ የቁጥጥር እና ምላሽ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል ።

ከህብረተሰብ ጤና ስጋቶች ውስጥ የፖሊዮ ቫይረስ አንዱ ሲሆን ሕፃናትን ለህመም፣ ለሞትና ለዘላቂ አካል ጉዳተኛነት የሚዳርግ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ በሽታ አምጪ ተህዋስ ነው፡፡ ፖሊዮ በሽታን መከላከል የሚቻለው ህፃናትን በመደበኛ የክትባት መርሃ ግብር እና በዘመቻ መልክ የሚሰጠውን የማጠናከሪያ ክትባት በአግባቡ እንዲከተቡ በማድረግ ነው፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ የዋይልድ ፖሊዮ በሽታ በአፍሪካ አህጉር መጥፋቱ ማረጋገጫ የተሰጠ ሲሆን አገራችን ኢትዮጵያም የምጨረሻዉን የዋይልድ ፖልዮ ቫይረስ ጥር ወር 2006 ዓ.ም ሪፖርት ያደረገች ሞሆኑ እና በ2009 ዓ.ም ከዋይልድ ፖሊዮ ነፃ መሆኗን በአፍሪካ ደረጃ የተቋቋመ ኮሚቴ የተረጋገጠ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን  በአጎራባች ሀገሮች ሲዘዋወር የቆየ በክትባት እጥረት የሚመጣዉ የፖሊዮ ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ በግንቦት ወር 2011 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን ቦህ ወረዳ የተገኘ ቢሆንም ተመሳሳይ የሆነ የፖሊዮ ቫይረስ ዝርያ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ተገኝቷል፡፡
በአጠቃላይ በአገራችን ኢትዮጵያ ከታህሳስ፣2011 ጀምሮ አስከ አሁን ድረስ በተሰራ ቅኝት ሌላ ዝርያ በክትባት እጥረት የሚመጣዉ ፖሊዮ በሽታ ከሰው ከተወሰደ ናሙና 32 እና ከአካባቢ ከተወሰደ ናሙና 3 የፖሊዮ በሽታ አምጭ ተህዋስ ተገኝቷል፡፡
የፖሊዮ ወረርሽኝ የሚከሰትበት ዋና ዋና ምክንያቶች ስንመለከት  በአካባቢው የመደበኛ ክትባት አገልግሎት ተደራሽነትና ተጠቃሚነት ዝቅተኛ መሆን እና ከፍተኛ የሆነ የክትባት አገልግሎት መጠን ማቋረጥ መኖሩ ነው፡፡ እስካሁን ድርስ የተሰጡ የመከላከያና መቆጣጠሪያ እርምጃዎች በተመለከተ ሱማሌ ክልል አምስት ዞኖች የመጀመሪው ዙር ዘመቻ ላይ 197,142 ከ5 አመት በታች ለሆኑት እንዲሁም በሁለተኛና ሶስተኛ ዙር የክትባት ዘመቻ ለ 588,879 ህፃናት ተሰቷል፡፡ በደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች በሶስት ዙር የክትባት ዘመቻ , የመጀመሪው ዙር  ዘመቻ በ11 ወረዳዎች ለ 245,179 ህፃናት እንዲሁም በሁለተኛና ሶስተኛ ዙር በ79 ወረዳዎች ለ 1,849,793 እድሜያቸው ከ5 አመት በታች ለሆኑት ህፃናት ተሰቷል፡፡እንዲሁም ከክትባቱ በተጨማሪ የቅኝትና አሰሳ ስርዓትን ማጠናከር ጨምሮ የተለያዩ የመከለከያና መቆጣጠሪያ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ
አሁን የሚሰጠው ዘመቻ የሚካሄድበት ጊዜ እና መንገድ በተመለከተ የፖሊዮ በሽታ ስርጭትን ለመግታት፣ ለማጥፋት እንዲሁም የህጻናትን የበሽታ መከላከል አቅም ለማጎልበት ከመስከረም 27-30 ቀን 2013 ዓ.ም ለተከታታይ 4 ቀናት በአራት ክልሎችና (ሶማሌ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ሃረሪ) በሁለት ከተማ አስተዳደሮች (አዲስ አበባና ድሬዳዋ) በሚገኙ 47 ዞኖች 334 ወረዳዎች የፖሊዮ ክትባት በዘመቻ መልክ ቤት ለቤት በሚደረግ ጉብኝት ለ ሰባት ሚሊዮን የሚሆኑ ህፃናት ይሰጣል፡፡ ስለሆነም የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ እድሜአቸው ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ህፃናት ከአሁን በፊት ክትባቱን ቢከተቡም ባይከተቡም አሁን የሚሰጠውን የፖሊዮ ክትባት መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የካቲት 24 2012 በደቡብ ብሄር በሄረሰቦች ክልል በተከሰተዉ የቢጫ ወባ ወረርሽኝ 86 ሰዎች በበሽታዉ መያዛቸዉ እና 4 ሰዎች መሞታቸዉ የሚታወቅ ሲሆን ወረርሽኙን ተከትሎ በተከሰተበት ወረዳ ክትባትን ጨምሮ በተሰጠዉ ምላሽ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ተችሏል፡፡ ሆኖም ግን በአሁኑ ሰአት በአካባቢዉ አሁንም ለወረርሽኙ ስጋት የሆኑ መንስኤዎች ስላሉ በደቡብ ክልል 11 ወረዳዎች እና አንድ የኦሮሞ አጎራባች ወረዳ ጨምሮ በአጠቃላይ በ 12 ወረዳ የሚኖሩ 704,000 ከ ጥቅምት 13 ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት በመከናነወን ላየረ ይገኛል፡፡  
ለዘመቻው አተገባበር ስኬታማነት እና የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የሀይማኖት አባቶች፣ የጎሳ መሪዎች፣ የአካባቢ ሽማግሌዎች፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በክትባቱ ዘመቻ የተለመደውን ትብብር እንዲያደርጉ እያሳሰብሁ ክትባቱ ቤት ለቤት የሚካሄድ ሲሆን የጤና ባለሙዎች ቤት ለቤት ክትባቱን ሲካሂዱ ሌሎች ጤና እና ጤና ነክ ችግሮችን ቅኝት ማለትም( የፖልዮ፣ የኩፍኝ፣የኮሮና፣የምግብ እጥረት ወዘተ) ስለሚሰሩ ህብረተሰቡ አስፈላጊዉን እገዛ እንዲደርግ ከወዲሁ እሳሰበኩ በተጨማሪም በዚህ ዘመቻ ወቅት የክትባት አገልግሎቱን የሚሰጡ ጤና ባለሙያዎች እና የህፃናት ወላጆች ወይም ተንከባካቢዎች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያስችል የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ፣ እጅን በሳሙናና በውሃ መታጠብ ወይም ሳኒታይዘር መጠቀም፣ ርቀትን መጠበቅ እንዲሁም ሌሎች የኮሮና በሽታን ለመከላከል የሚያስችሉ ዜደዎችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ አሳስባለሁ፡፡
ህጻናትን በማስከተብ ፖሊዮን እንከላከል፡፡
                                                              መስከረም 22 ቀን 2013 ዓ.ም