የኮቪድ 19 በአለም አቀፍ ደረጃ እንደተከሰተ የመተላለፊያ እና የመከላከያ መንገዶቹን በተጨባጭና በተረጋገጠ መልኩ ማወቅ ባለመቻሉ የመከላከያና የመቆጣጠሪያ መንገዶችን ተግባራዊ ለማድረግ ፈታኝ አድርጎታል፡፡ አሁንደግሞ የኮቪድ 19 ዓለምን በሙሉ ባዳረሰበት ወቅት በቫይረሱ ከሚያዙት ሰዎች 85 በመቶ የሚሆኑት ምንም አይነት የቫይረሱ ምልክት ያልታየባቸው በመሆናቸው በሕብረተሰቡ ዘንድ የኮቪድ 19 እንደሌለና ውሸት እንደሆነ የሚያሳይ የተሳሳተ አመለካከት እንዲፈጠር እያደረገ ይገኛል፡፡
ታዲያ ይህ አመለካከት በጤና ባለሙያዎች እና ከኮቪድ 19 ተይዘው ካገገሙ ግለሰቦች እይታ አንጻር ሲታይ ምን ይመስላል?
ዶ/ር ፌቨን ግርማ በሰሜን ሸዋ ዞን መስተዳድር በደብረብርሃን ከተማ በጠባሴ የኮቪድ 19 የህክምና መስጫ ማዕከል የጽኑ ህሙማን ህክምና ባለሙያ የታዘቡትን ሲገልጹ በማዕከሉ ለመታከም የሚመጡት ሰዎች በሙሉ በጽኑ ህመም ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡በበሽታው የተያዙ ሰውች ስቃያቸውን ማየት እጅግ ያሳዝናል፤ በተለይ ተጓዳኝ በሽታዎች ያሉባቸው ታካሚዎች ስቃያቸው የጠነከረ ነው፡፡አንዳንድ ሰዎች ኮሮና እንደሌለ ይናገራሉ፣ ጥንቃቄዎችንም ተግባራዊ ከማድረግ ታቅበዋል ነገር ግን በጽኑ ህሙማን ማከሚያ ማዕከል የሚገለገሉ ታካሚዎች መተንፈስ አቅቷቸው ስቃያቸው በዝቶ ህይወታቸው ጭምር እያለፈ ይገኛል ለዚህም እኔ እራሴ ማስረጃ ነኝ ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
ዶ/ር ፌቨን በማብራሪያቸው፤የኮሮና ቫይረስ በህመም መሰቃየትና ሞትን ብቻ አይደለም እየፈጠረ ያለው ችግር ለምሳሌ ተማሪዎች በኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ምክንያት ሳይማሩ ብዙ ጊዜ መቀመጣቸው ለተለያዩ የስነ-ልቦና ጫናዎች ተዳርገዋል፤ በሌላ ኩል ደግሞ በሃገርም ላይ ከፍተኛ የኤኮኖሚ ኪሳራ እያደረሰ ይገኛል፡፡ስለዚህ ሰው ሰርቶ እራሱን መመገብ ስላለበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመነሳት ጉዳይ አስገዳጅ ሆኗል፡፡ በቀጣይም ትምህርት ቤቶች መከፈታቸው ግዴታ ነው፤ ነገር ግን መደረግ የሚገባቸውን የመከላከያ ጥንቃቄዎችን በትኩረት ተግባራዊ ካልሆኑ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መጨመሩ የማይቀር ችግር ነው፡፡በመሆኑም ማንኛውም ስው የጥንቃቄ መንገዶችን ሳይሰላችና በግዴለሽነት አመለካከት ውስጥ ሳይገባ የመከላከያ መንገዶችን በሚገባ ሊተገብር ይገባል፡፡ይህ ካልሆነ ግን ለሁላችንም ከፍተኛ ችግር ነው በማለት ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
አቶ መሰረት አወቀ ከላይ በተጠቀሰው የኮሮና ቫይረስ ማዕከል የጽኑ ህሙማን ባለሙያ ሲሆኑ የታዘቡትን እንዲህ ይገልጻሉ፤ ከሚታየው የሕብረተሰቡ የጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ የኮሮና ቫይስ በሽታ በቀላሉ ሊቆም አይችልም ምክንያቱም ሕብረተሰቡ ቫይረሱን ንቆታል፣በራሱ ላይ ሞትን የወሰነ ይመስላል፣ ማንኛውንም እንቅስቃሴ የሚያደርገው በግዴለሽነት ነው፡፡ነገር ግን የበሽታውን ከባድነትንና የሚፈጥረውን አሰከፊ ተጽዕኖ ማየት የቻልነው እኛ ከታካሚዎቹ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለን የጤና ባለሙያዎች ነን፡፡ ስለዚህ የጥንቃቄ መንገዶችን ለመተግበር ዳተኝነትን ከማሳየት ይልቅ እራስን በመጠበቅ ህይወትን መታደግ ይገባዋል ይላሉ፡፡
የሁለቱን ባለሙያዎች ሃሳብ በመጋራት የድጋፍ ሃሳባቸውን የሚያቀርቡት ደግሞ በምንጃር ሸንኮራ በሃረርቲ ከተማ የሚገኙት በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ከብዙ ስቃይ በኋላ በዚሁ ማዕከል ያገገሙ ሳጅን ነፍሴ የልዩ ሃይል አባል ናቸው፡፡በሳቸውም አገላለጽ የኮሮና ቫይረስ በሽታ የለም በማለት ከጥንቃቄ ውጪ በሆነ መልኩ በየጠላቤቱና በየአረቄ ቤት እየዞርኩ ስጠጣ ነበር ነገር ግን በበቫይረሱ ተይዤ ከብዙ ስቃይ በኋላ በጤና ባለሙያዎችና በመሳሪያ ድጋፍ ልድን ችያለሁ ስለዚህ ከዚህ በኋላ እየዞርኩ ኮሮና መኖሩንና አስከፊ በሽታ መሆኑን ከኔ እንዲማሩ አደርጋለሁ ሲሉ ሃሳባቸውን ይገልጻሉ፡፡
በመሆኑም መተንፈስ ተስኖን ስቃያችን በዝቶ ለአደጋና ለሞት ከመጋለጣችን በፊት ለራሳችን፣ ለቤተሰባችንና ለወገኖቻችን ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡