የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ማስተባበሪያ ማእከል በሃገር አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ በሽታን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት በሁሉም የሃገሪቱ ክፍል የአስከሬን አያያዝ ላይ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ወረርሺኙን ለመግታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገለጸ፡፡
አቶ አስቻለው አባይነህ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አሁን ስላለው የአስከሬን አቀባበር አስመልክቶ እንደገለጹት በቀብር ስነ-ስርዓት ወቅት በርካታ ሰዎች ከተለያዩ ቦታዎች ስለሚመጡ የኮሮና ቫይረስን በማስተላለፍ በኩል የተለያዩ አጋጣሚዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ፤ይህ ደግሞ ችግር ላይ የሚወድቁ ሌሎች ሰዎችን መፍጠር ስለሚሆን የቀብር ስነ-ስርዓት ሲፈጸም ህብረተሰቡ በእስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ የተቀመጡትን መመሪያዎች በሚገባ በመገንዘብ ፣ተገቢውን ጥንቃቄ በመውሰድ ተግባራዊ ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ የአስከሬን የቅብር ስነ-ስርዓት ላይ በሚኖሩ የተለያዩ ንክኪዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ከፍተኛ እንዳይሆን በሃገር አቀፍ ደረጃ ማንኛውም የሞተ ሰው የቅብር ስነ-ስርዓት ከመካሄዱ አስቀድሞ የኮሮና ቫይስ የላቡራቶሪ ናሙና መወሰድ እንዳለበት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል፣የሃይማኖት አባቶች እና የቅብር አስፈጻሚ ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊገነዘቡት እንደሚገባ ዳይሬክተሩ አያይዘው ገልጸዋል፡፡
ዳይሬክተሩ በተጨማሪም እንደተናገሩት ከዚህ በፊት የቀብር ስነ-ስርዓት ለማድረግ የኮቪድ 19 ምርመራ ውጤት እስኪመጣ ይጠበቅ የነበረው መመሪያ ተሻሽሎ ከሰኔ 11/2012 ዓ.ም ጀምሮ ያለውን የቅብር መዘግየት፣የማህብረሰቡን ቅሬታ ታሳቢ በማድረግ የአስከሬን ናሙና እንደተወሰደ የቀብር ስነ-ስርዓት እንዲፈጸም መደረጉን ገልጸው፤በአዲስ አበባ ከተማ የአስከሬን ምርመራ ከተጀምረበት ከሰኔ መጀመሪያ አካባቢ ጀምሮ እስከ ሀምሌ 30/ 2012 ዓ.ም በአጠቃላይ 1827 የአስከሬን የላቦራቶሪ ምርመራ መደረጉን እና 176 የሚሆኑት የኮሮና ቫይረስ እንደነበረባቸው እንዲሁም 1651 የሚሆኑት ደግሞ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው አብራርተዋል፡፡
ከጤና ተቋማት ውጪ ሞት በሚከሰቱ ጊዜ ኮቪድ -19 ን ለመከላከል የሚደረጉ ጥንቃቄዎች
ከጤና ተቋማት ውጪ ሞት በሚከሰት ወቅት የአስከሬን ግነዛ፣አስከሬን የማጓጓዝ ፣የመቅበር እና የሃዘን ስነ-ስርዓት ላይ የሚደረጉ የሟች ቤተሰቦችና አስከሬን የሚገንዙ ሰዎች ሊያደርጓቸው የሚገቡ ጥንቀቄዎች እና ግዴታዎች በአስቸኳይ ጊዜያዊ አዋጅ መሰረት የኮቪድን -19 ወረርሽን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚከተሉትን ተግባራት ተፈፃሚ ሊሆኑ ይገባል፡፡
• ለጤና ተቋም ማሳወቅ አስከሬኑ የኮቪድ-19 ላቡራቶሪ ናሙና እንዲወሰድ ማድረግ
• አስከሬን የሚገንዙ ሰዎች የእጅ ጓንት፣የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ወይም ከፕላስቲክ የተሰራ ጓንት እና መነጽር እንዲለብሱ ማድረግ
• ሀኪሞች በሌሉባቸው አስከሬን ለማጓጓዝ ተገቢውን ጥንቃቄ ለማድረግ በሚችሉ ሰዎች ብቻ እንዲከናዎን ማድረግ
• ኮቪድ 19 ምልክት የሚታይባቸው ሰዎች አስከሬን ከሚያጓጉዙ ሰዎች ጋር እንዳይሳተፉ ማድረግ
• በቀብር ስነ-ስርዓቱ ላይ የሚገኙ ሰዎች ሁሉ ሁለት የአዋቂ እርምጃ በመራራቅ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ እንዲሁም አስከሬኑንም ሆነ አስከሬኑ ያለበትን ሳጥን ያለመነካካትና ያለመሳም
• አስከሬን ከተጫነ በኋላ የሰውነት መከላከያ አልባሳት በመልበስ አስከሬን ያለበትን ሳጥን ፣አስከሬን የገነዙትን ሆነ አስከሬኑ የነካካቸውን ቦታዎች ወይም ቁሳቁሶች፣ሟቹ የነበረበትን አልጋ፣የተለያዩ የመገልገያ እቃዎች፣የቤቱን ወለል ፣የተጓዘበትን መኪና እና አጠቃላይ እቃዎች በበረኪና ውህድ እንዲጸዳ ማድረግ
• አስከሬን የሚያጓጉዙ ሰዎች ጓንት ማድረግ የግድ ሲሆን በጓንታቸው የተለያዩ እቃዎችን ያለመነካካት እና አስከሬኑን ከቦታ ወደ ቦታ አለማንቀሳቀስ
• አስከሬን ከግነዙትም ሆነ ከሟች ቢተሰቦች ሁለት የአዋቂ እርምጃ መራቅ እንዳለ ሆኖ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ መጠቀም
• የሟች ቤተሰቦች በተቻለ መጠን አስከሬኑን በሞተበት አካባቢ መቅበር ይኖርባቸዋል፤ወደ ሌላ ቦታ የማጓጓዝ ግዴታ በሚፈጠርበት ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡
• የእምነት ተቋማት ሃላፊዋች እና የሃይማኖት አባቶች አስከሬኑ ወደ ቀብር ቦታ ከመምጣቱ በፊት የኮቪድ-19 የላቦራቶሪ የምርመራ ናሙና መወሰዱን የማረጋገጥ ግዴታ አለባቸው፡፡
• በቀብር ስነ-ስርዓቱ ወቅት ከ50 የማይበልጡ ሰዎች መሆናቸውን መከታታል እና ከጤና ተቋማት የሚሰጡ መመሪያዎችን መከታተልና ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው