ለኮቪድ-19 መከላከያ የሚሆን ደህንነቱ የተረጋገጠና ውጤታማ የሆነ ክትባት በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል እስከ መጭው የአውሮፓውያን አመት አጋማሽ ላይደርስ እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።
ሰዎች ክትባቱ ፈጥኖ ሊደርስልን ነው የሚለውን ጉጉትና ተስፋ በልክ እንዲያደርጉ የጤና ባለስልጣናት እየመከሩ ይገኛሉ።
በጤና ላይ አደጋ የማያስከትልና በደንብ ውጤት የሚያመጣ ክትባት እንደዚሁ በይድረስ ይድረስ ተቻኩሎ መስራት የሚሆን አይደለም፤ጊዜ ይጠይቃልም ብለዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ክትባት ፍለጋው በተገቢው መንገድ የማከናወኑ ሂደት በደንብ እየተካሄደ እንደሆነ እየገለፀ ነው።
ከስድስት እስከ ዘጠኝ የሚደርሱ ክትባቶች በአሁኑ ጊዜ በሶስተኛ ምዕራፍ የሰው ሙከራ ደረጃ ላይ እንደሚገኙም አመልክቷል።
በእነዚህ በጥንቃቄ በተዘጋጁት ሙከራዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እየተሳተፉ መሆናቸው የWHO ቃል አቀባይ ማርጋሬት ሃሪስ ገልፀዋል።
የኮሮና ቫይረስ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ከመፈቀዱ በፊት የጤና ስጋት የማያስከትልና ቢያንስ በሙከራው ከሚሳተፉት 50 በመቶውን ከቫይረሱ መከላከል መቻሉ መረጋገጥ አለበት ሲሉ አሳስበዋል።
አያይዘው በተጨባጭ ያለውን ሁኔታ ካየን ከመጭው የአውሮፓውያን 2020/2021 አጋማሽ በፊት ክትባት ለህዝብ መስጠት ይጀመራል ብለን አንጠብቅም ብለዋል።
ከዚህ ባለፈም ቃል አቀባይ ማርጋሬት ሃሪስ ለቬኦኤ እንደተናገሩት መንግስታት ክትባት መቼ በአጣዳፊ ሁኔታ ወይም ለአጠቃላይ ጥቅም እንደሚያውሉ WHO አይነግራቸውም የየራሳቸውን ውሳኔ መውሰድ አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል። ነገር ግን ይህን ወረርሽኝ ድራሹን የሚያጠፋ ክትባት እየደረሰ ነው ብሎ ለህዝብ ያልሆነ ተስፋ መስጠት እንደማይገባ እናስጠነቅቃለን ማለታቸውን #ቪኦኤ ዘግቧል።