የጤና ጥበቃ ሚንስትሩ ዶ/ር አሚር አማን የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ሞዴስን ከቀረጥ ነፃ ለማድረግ እየሠሩ እንደሆነ ለቢቢሲ ገለጹ።
የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ (ሞዴስ) በተመጣጠነ ዋጋ እንዲቀርብ እንዲሁም ተደራሽነቱ እንዲሰፋ አንዱ እርምጃ ከቀረጥ ነፃ ማድረግ እንደሆነ ሚንስትሩ አስረድተዋል። የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ እንደማንኛውም መድኃኒት እና የህክምና አገልግሎት መስጫ መሣሪያ ተመርቶ እንዲሰራጭ ለማድረግ እቅድ እንደተያዘም ገልጸዋል።
ዶ/ር አሚን እንዳሉት፤ የደረሱበትን ውሳኔ በሚመጣው አዲስ ዓመት ከፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ከሚመለከታቸው ተቋሞች ጋር በመሆን ለሕዝብ ይፋ ያደርጋሉ።
"በግሌና እንደ ጤና ጥበቃ ሚንስትርነቴም፤ የንፅህና መጠበቂያ ማግኘት የእያንዳንዷ ሴት መብት መሆኑን አምናለሁ" ያሉት ዶ/ር አሚን፤ መንግሥት ለሴቶች የንፅህና መጠበቂያ የማቅረብ ኃላፊነት እንዳለበትም ገልጸዋል።
ሚንስትሩ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ መንግሥት ለአቅመ ደካማ ሴቶች የንፅህና መጠበቂያ በነፃ የማቅረብ ኃላፊነት እንዳለበት አስረድተዋል። የንፅህና መጠበቂያ መግዛት ለሚችሉ ሴቶች ደግሞ ምርቱ በተመጣጠነ ዋጋ ገበያ ላይ መቅረብ እንዳለበት አክለዋል።
የንፅህና መጠበቂያ አለማግኘት በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና እንዲሁም በትምህርት ላይም ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል።
የጤና ጥበቃ ሚንስትሩ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የኢቦላ ወረርሺኝ ቢከሰት በአፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ ቡድን እንደተቋቋመም ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ፣ በድሬ ዳዋ እና በመቐለ አውሮፕላን ማረፊያዎች በኩል ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ግለሰቦች ላይ የኢቦላ ምርመራ እንደሚደረግም ሚንስትሩ አክለዋል። ከአውሮፕላን ማረፊያዎቹ በተጨማሪ በ28 ኬላዎች ላይም ምርመራው ይካሄዳል።
"ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚመጡ ሰዎችን የጤና ሁኔታ የሚከታተል ቡድን አዋቅረናል። ሰዎቹ ወደ አገር ውስጥ ከገቡበት ቀን ጀምሮ ለአሥር ቀናት ክትትል ይደረጋል" ሲሉ አስረድተዋል።
ዶ/ር አሚር እንዳሉት፤ ኢቦላን ለመከላከል እንቅስቃሴ የተጀመረው ከአምስት ዓመት በፊት ነበር። በወቅቱ ቫይረሱ በምዕራብ አፍሪካ አገራት አሳሳቢ ከነበሩ ወረርሽኞች ግንባር ቀደሙ ስለነበር ኢትዮጵያ የህክምና ባለሙያዎችን ወደ ምዕራብ አፍሪካ አገራት ልካ ነበር።
"ባለሙያዎቹን የላክናቸው አገራቱን ከማገዝ ጎን ለጎን ኢትዮጵያን ከወረርሽኙ ለመከላከል ምን ማድረግ እንዳለብን ትምህርት ቀስመው እንዲመጡ ጭምርም ነበር" ሲሉ ተናግረዋል።
የህክምና ባለሙያዎቹ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ፤ ወረርሽኙ ድንገት ቢከሰት በአፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ ቡድን መዋቀሩን ገልጸዋል። በአሁን ወቅት ኢቦላ በተለይም በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከፍተኛ ቀውስ መፍጠሩን ተከትሎ ይህ ቡድን በተጠንቀቅ እየጠበቀ መሆኑንም አክለዋል።
ወረርሽኙ ቢከሰት በቫይረሱ የተያዙ ግለሰቦች ተለይተው ክትትል የሚደረግበት ልዩ ቦታ በአዲስ አበባ ይገኛል። በክልል ከተሞችም ይህንን አገልግሎት የሚሰጡ 11 ልዩ ቦታዎች መዘጋጀታቸውንም ሚንስትሩ ገልጸዋል።