ጨው በተለምዶ ሶዲየም ክሎራይድ (NaCl) ተብሎ የሚጠራዉ ነዉ፤ ጨዉ የሶድያምና የክሎራይድ ንጥረነገሮች ዉህድ ሲሆን በዉስጡም 40 በመቶ ሶድየምና 60 በመቶ ክሎራይድን ይይዛል፡፡በሌላ አነጋገር 2.5 ግራም ጨዉ 1 ግራም ሶድየምና 1.5 ግራም ክሎራይድ ይይዛል ማለት ነዉ፡፡
ጨዉ ምግብን ለማጣፈጥና ለማቆየት ለሺህ ዘመናት ጥቅም ላይ ዉሏል፡፡ ሁላችንም ለጤንነታችን ጥቂት ጨው እንፈልጋለን ግን ብዙ ጨዉ መብላት የደም ግፊታችንን ከፍ ያደርገዋል ፣ ለልብ ህመም የመጋለጥ እድላችንን ይጨምራል
ሰዉነታችን ጨዉን ለምን አገልግሎት ይፈልጋል?
ለብዙ የሰውነት ተግባራት ሁለቱም ማለትም ሶዲየም እና ክሎራይድ በጣም አስፈላጊ ናቸው ፡፡ ጨዉ የደም ግፊትን ለማስተካከል ፣ የሰዉነት ፈሳሽ ምጣኔን ለመቆጣጠር ፣ የጡንቻ እና የነርቭ ተግባራት ትክክለኛ ሁኔታዎችን እንዲጠብቁ እንዲሁም በሰዉነታችን ሴሎች/ህዋሶች ሽፋን ውስጥ አልሚ ንጥረ ነገሮችን ለመምጠጥ እና ለማጓጓዝ ይረዳል፡፡ በተጨማሪም ክሎራይድ በጨጓራችን ዉስጥ ምግብን ለመፍጨት የሚያገለግለዉን ሃይድሮክሎራይ አሲድን( hydrochloric acid, HCl) ለማምረት ያገለግላል፡፡
አንድ ሰዉ በቀን ምን ያህል ጨዉ መመገብ አለበት?
አንድ ሰዉ በቀን ምን ያህል ጨው ዕለት ተዕለት መገብ ስለሚገባዉ ትክክለኛው መጠን /መስፈርት ባይታወቅም በየቀኑ ከ1.25 ግ እስከ 2.5 ግ (ከ0.5 እስከ 1 ግ ሶዲየም) መመገብ ተገቢ ነዉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ ጨው በብዙ የተለያዩ ምግቦች ውስጥ ስለሚገኝ ሰዎች የጨዉ መጠን ማነስ ላይገጥማቸዉ ይችላል፡፡
እንደ የአለም ጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ በቀን ዉስጥ ከፍተኛ የሆነ የሶድየም ፍጆታ ( ማለትም በቀን ከ2 ግራም በላይ ሶድየም ወይም በሌላ አነጋገር ከ5 ግራም በላይ ጨዉ በቀን ዉስጥ መመገብ) ና አነስተኛ የሆነ ፖታሲየም ( ከ3.5 ግራም በቀን በታች) መመገብ ለደም ግፊት አስተዋፅዖ ያበረክታል፤ እንዲሁም ለልብ ህመም እና ለስትሮክ ተጋላጭነትን ይጨምራል፡፡ ብዙ ሰዎች በጣም ብዙ ጨው ይጠቀማሉ ማለትም በቀን በአማካይ ከ 9 እስከ 12 ግራም ይህም ማለት በቀን መዉሰድ ከሚመከረው ከፍተኛዉ መጠን በእጥፍ ያህል ማለት ነዉ።
ለአዋቂዎች በቀን ከ 5 ግራም በታች ጨው መመገብ የደም ግፊትን እና የልብና የደም ሥር (cardiovascular) በሽታን ለመቀነስ ይረዳል ፣ የደም ቧንቧ እና የደም ቧንቧ ህመም አደጋን ለመቀነስ ይረዳል ፡፡ የጨው መጠንን የመቀነስ ዋነኛው ጥቅም ከደም ግፊት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ቅነሳ እንዲኖር ይረዳል፡፡
የጨው መጠንን መቀነስ የህዝብን ጤና ለማሻሻል የሚረዱ በጣም ወጭ ቆጣቢ እርምጃዎች ዉስጥ አንዱ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን ጨዉን መቀነስ ጤናማ ህይወትን ለመምራት ይረዳል፡፡ እንደ አለም ጤና ድርጅት መረጃ የዓለም የጨው ፍጆታ ወደ ሚመከረው ደረጃ ከቀነሰ በየአመቱ 2.5 ሚሊዮን የሚገመት ሞት መከላከል ይቻላል፡፡