ዕድሜያቸው ከ30-40 ዓመት የሆኑ ሰዎች የሐኪም ፊት እንዲያዩ ከሚያስገድዳቸው ወይም ስራ ከሚቀሩባቸው ምክንያቶች አንዱ የጀርባ ሕመም ነው፡፡
በዚህ ዕድሜ የጀርባ ሕመም የተለመደ አለም አቀፍ የጤና ችግር ከመሆኑም በተጨማሪ ለአካል ጉዳት ከሚዳርጉ ምክንያቶች መካከል አንዱም ነው፡፡ ሌላው አስደንጋጭ መረጃ ብዙ ሰዎች በዕድሜ ዘመናቸው ቢያንስ አንዴ በጀርባ ሕመም መጠቃታቸው ነው፡፡ ይሁንና እንደመታደል ሆኖ የጀርባ ሕመምን ለመከላከለም ሆነ ሕመሙ ሲያጋጥም በፍጥነት ከሕመሙ ለመውጣት የሚያስችሉ የቤት ውስጥ ሕክምናዎችን ጨምሮ የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል በሳምንት ውስጥ ፈውስን የሚያስገኝ ቢሆንም ሕመሙ በወራት የዘለቀ እንደሆነ ግን ችግሩ ከበድ ያለና የተለያዩ የጤና ችግሮች ውጤትም ሊሆን ይችላል፡፡
በተደጋጋሚ ለጀርባ ሕመም የሚያጋልጡ ምክንያቶች
1. የጡንቻ ወይም የሊጋሜንቶች ውጥረት
2. ድንገተኛ የጡንቻ መኮማተር
3. የጡንቻ መሳሳብ ወይም ውጥረት
4. የዲስክ መጎዳት
5. አደጋዎች (ስብራት ወይም መውደቅ)
6. እርግዝና
7. በዕድሜ መግፋት
8. ከፍተኛ የሰውነት ክብደት
9. የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ
10. ሲጋራ ማጨስ
11. ካንሰርና የአንጓ ብግነት
12. የኩላሊት ጠጠር ወይም ኢንፌክሽን
13. ድባቴና ጭንቀት እንዲሁም የህብለ ሰረሰር በቀላሉ መሳሳብና ቀዳዳ መፍጠር ናቸው፡፡
የጀርባ ሕመም አባባሽ ምክንያቶች
1. ያለ አግባቡ ዕቃዎችን ማነሳት (ተጠማዞ፣ተንጠራርቶ እና ወገባችንን እና እግራችንን ወጥሮ ማንሳት)
2. ከባድ ነገሮችን ያለ አግባቡ ማንሳት
3. ድንገተኛና የማይመች እንቅስቃሴ ማድረግ
4. ረጅም ጊዜ መቆም ወይም መቀመጥ
5. ረጅም ሰዓት ያለ እረፍት መንዳት
6. ወገባችንን ከመቀመጫ መደገፊያ ጋር ለጥፎ ከመቀመጥ ይልቅ ጎብጦ መቀመጥ ናቸው፡፡
የጀርባ ሕመም መኖሩን የሚጠቁሙ ምልክቶች
1 .የጡንቻ ሕመም
2. ጀርባችንን የመውጋት ስሜት
3. ሕመሙ ወደ እግራችን የዘለቀ እንደሆነ
4. በሚያጎነብሱበት፣ዕቃ በሚያነሱበት፣በሚቆሙበትና በሚራመዱበት ጊዜ ሕመም መሰማት
5. ጋደም በምንልበት ጊዜ የሕመም ሁኔታ መሻሻል ናቸው፡፡