ወላጆች ለልጆቻቸዉ ያላቸዉን ፍቅር ሊያሳዩባቸዉ የሚችሉባቸዉ የተለያዩ የፍቅር መግለጫ መንገዶች አሉ፡፡
እያንዳንዱ ልጅ ፍቅር የሚቀበልበት የራሱ የሆነ መንገድ አለዉ፡፡ የልጃችን ምርጫ የሆነውን ይህን መንገድ ማወቅ ከልጆቻችን ጋር ለሚኖረን ግንኙነት ብሎም ለልጆቻችን ጤናማ አስተዳደግ ወሳኝ ነዉ፡፡
ምንም ‘ንኳን ማቀፍና መሳም ፍቅርን የምንገልጽበት የተለመደዉ መንገድ ቢሆንም ሌሎችም አማራጮች አሉ፡፡ አንዳንድ አባቶች ልጆቻቸዉን አቅፈው ወደ ላይ እየወረወሩ ያጫዉታሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ እጅና እጃቸዉን ይዘዉ እያዞሩ ያጫዉቷቸዋል፡፡ እናት ደግሞ ልጇን አቅፋ መጽሃፍ ታነብላታለች፡፡ በንዲህ መሰል አካላዊ ንክኪ የሚገለጽን ፍቅር የበለጠ የሚረዱ ልጆች “እወድሻለሁ” ከሚባሉ፣ ወይም አሻንጉሊት ከሚገዛላቸዉ፣ ይሄን ማቀፍ፣ መሳም፣ ወዘተ እጅጉን ይመርጡታል፡፡
ያ ማለት ሌሎቹን የፍቅር መግለጫ መንገዶች አይፈልጉም ሳይሆን ወደየትኛው የበለጠ እንደሚያደሉ ለማሳየት ነዉ፡፡ ያለ መሳም፣ ማቀፍ፣ ጀርባን አሸት አሸት ማድረግ ሌሎቹ ቢኖሩም የፍቅር ባትሪያቸዉ ጎዶሎ ይሆናል፡፡
ከልጆቻችን ጋር በምናደርገዉ ንግግር ፍቅራችንን ስንነግራቸዉ፣ ስናበረታታቸዉና፣ ስናሞግሳቸዉ ልጆቻችንን እንደምንወዳቸዉ ይረዳሉ፡፡
እነዚህ ቃሎች በፍጥነትና በቀላሉ ከአፍ የሚወጡ ቢሆኑም በቀላሉ አይረሱም፡፡ በህይወታቸዉ ዘመን ሁሉ ያስታዉሱታል፡፡ ለሚኖራቸዉ በራስ መተማመንና ዉስጣዊ ሰላም ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡
ሌላኛዉ ለልጆቻችን ፍቅር የምንገልጽበት መንገድ ከልጆቻችን ጋር የምናሳልፈዉ ጊዜ ነዉ፡፡ ይህ ታዲያ ሳሎን ሆነን እነሱ የቤት ስራቸዉን ሲሰሩ እኛ ቴሌቪዥን ማየት ማለት አይደለም፡፡ ሃሳባችን ሳይከፋፈል ሙሉ ትኩረታችንን ሰጥተን አብረናቸዉ ስንጫወት ለልጆቻችን የምናስተላልፈዉ መልእክት “ካንተ ወይም ካንቺ ጋር መሆን ደስ ይለኛል፡፡ አንቺ/አንተ ለኔ በጣም አስፈላጊ ናችሁ” የሚል ነዉ፡፡ አብረናቸዉ ጊዜ ስናሳልፍ ዋናዉ ቁምነገር የምናደርጋቸዉን ነገሮች አብሮ ማድረጋችን እንጂ የግድ አይስክሬም መጋበዝ ወይም ውድ መጫወቻ ቦታ መሄድ ማለት አይደለም፡፡
ለልጆቻችን ምግብ፣ ዉሃ፣ ትምህርት፣ መጠለያ፣ ወዘተ ከሟሟላት ባለፈ አብረናቸዉ በቂ ጊዜ ልናሳልፍ ይገባል፡፡ ይሄም ለልጆቻችን የወላጅ ፍቅርን በበቂ ሁኔታ ሰጥተን የተረጋጉና በራሳቸዉ የሚተማመኑ እንዲሆኑ ከማገዙ ባለፈ በመልካም ስነምግባር ታንጸዉ እንዲያድጉ ይረዳል። ያንን ካላደረግን እኛ የኪራይ፣ የትምህርት ቤት፣ የምግብ እንከፍላለን እንጂ ልጆቻችንን ቴሊቪዥንና ሌላ ሰዉ ነዉ የሚያሳድግልን!
ለልጆቻችን ስጦታ መስጠት ሌላኛዉ የፍቅራችን መግለጫ መንገድ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደስጦታው አይነት ወዲያው ሲሰጥ ብቻ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ ቆይቶም ቢሆን ፍቅራችሁን ያስታዉሳቸዋል፡፡ ልጆችም ሆኑ ትልልቅ ሰዎች ስጦታ የሚወዱ ቢሆንም ዋናዉ የፍቅር ቋንቋቸዉ ስጦታ ለሆኑ ልጆች ልዩ ትርጉም አለዉ፡፡
የልጆቻችሁን ፍላጎትና ምርጫ ተረድታችሁ ሳትጠየቁ በፊት ማድረግም ፍቅራችሁን የበለጠ ሊያሳይ ይችላል፡፡ የሆነ ነገር ግዙልን ባሉ ቁጥር ወደ ሱቅ መሮጥ እየመከርን አይደለም፡፡ እንዲያ ካስቸገሯችሁ በጊዜ “አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነዉ!” የሚለዉ ዘፈን አሰሟቸዉ! በመጨረሻ የምናየው የፍቅር መግለጫ መንገድ ልጆቻችንን በሚያስፈልጋቸዉ ሁሉ መርዳት ነዉ፡፡ ለምሳሌ ልጃችሁ ሳይክሌን ስራልኝ፣ አሻንጉሊቴን አስተካክይልኝ ወዘተ ሲሉ ፍቅራችንን የምናሳይበት ጥሩ አጋጣሚ ነዉ፡፡ የልጆቻችንን ጥያቄ ለሟሟላት የሚያስችል አቅምና ጊዜ ካለን ቢያንስ የተወሰኑትን ብናደርግ መልካም ነዉ፡፡ ለምሳሌ፡ ሳይክሌን ስራልኝ ሲባል አንድ አባት ስራዉን ለሌላ ሰዉ (ተከፍሎም በነጻም) ከሚያስተላልፈዉ ከልጁ ጋር እያወራና እያሳየዉ ሳይክሉን ቢሰራዉ ለልጁ ያለዉን ፍቅር የሚያሳይበት ብቻ ሳይሆን ጥሩ ጓደኝነት የሚመሰርቱበትም አጋጣሚ ይሆናል ፡፡ ያ ማለት ራሳቸዉም ሊሰሩ የሚችሉትን ነገር ሁሉ በጠየቋችሁ ጊዜ ሁሉ እያረጋችሁ ራሳቸውን
እንዳይችሉ እናርጋቸዉ ማለት ግን አይደለም፡፡
ልብ በሉ ልጅን በሚገባዉ መንገድ ለማሳደግ ምግባቸዉን መስጠትና ትምህርት ቤት ማስመዝገብ አይበቃም፡፡ ጠንካራ መንፈስና በራስ መተማመን እንዲኖራቸዉ “እንደምንወዳቸው” ማወቅ አለባቸዉ፡፡ “ወላጁ አይደለሁ ‘ንዴ! እንደምወደዉማ ያውቃል” ብለን መደምደም አንችልም፡፡ ከላይ የዳሰስናቸዉን የተለያዩ መንገዶች ግንዛቤው ዉስጥ አስገብተን
ልጆቻችንን በፍቅር እናንበሽብሻቸዉ! ያለነሱ ማን አለን!