የአእምሮ ህመም ምክንያቶች የተለያዩ ናቸው፤ ሆኖም ግን አብዛኛዎች የስነ-ህይወታዊ፣ የስነ-ልቦናዊ እና የማህበራዊ ችግሮች ስብጥር የሆነ መነሻ አላቸው፡፡
የአእምሮ ጤና ባለሞያዎች የአእምሮ ህመምን በተመለከተ ከላይ የተገለፁትን መንስኤዎች መስተጋብር አያያይዞ የሚያስረዳ “ስነህይወት-ስነልቦና እና ማህበራዊ (bio-psychosocial)” የተባለ ሞዴል አዘጋጅተዋል፡፡
ስነህይወታዊ፣ ስነልቦናዊ፣ ማህበረሰባዊ ጉዳዮች/ችግሮች አብዛኛዉን ጊዜ የመደራረብ ባህሪያት አላቸው፡፡ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የስነህይወት፣ የስነልቦና እንዲሁም የማህበራዊ የአእምሮ ህመም መንስዔዎች በምሳሌነት ቀርበዋል ፡-
1. ስነ-ህይወታዊ መንስኤዎች (biological causes): የተፈጥሮ/በዘር የሚወረስ- ይህም ማለት የአዕምሮ ህመም ካለበት ቤተሰብ ወደ ልጅ የመተላለፍ ወይም ደግሞ ልጆቹ ይበልጥ ተጋላጭ መሆን (ለምሳሌ እንደነ ስኪዞፍሬኒያ፣ ሽቅለት እና ድባቴ በቤተሰብ የመከሰት እድላቸዉ የሰፋ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ)፣ በአዕምሮ ውስጥ ያሉ ንጥረ ነገር (ኬሚካሎች) መዛባት፤ በጭንቅላት ላይ የደረሰ አደጋ፣ ሱስ አምጪ ንጥረ ነገሮችን መጠቀም (አልኮል መጠጣት ወይም ጫት መቃም ሌሎችንም ሱሶች መጠቀም፣ የምግብ እጥረት፣ ኢንፌክሽን አምጪ በሽታዎች ወዘተ…
2. ስነ-ልቦናዊ መንስኤዎች (psychological causes): እነዚህ መንስኤዎች ደግሞ ከአስተዳደግ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ሁኔታዎች ናቸዉ። ለምሳሌ፡- በልጅነት ጊዜ በቂ እንክብካቤ አለማግኘት፣ አብዝቶ መጨነቅ፣ የቤተሰብ መበታተን፣ በተረበሸ ቤተሰብ ዉስጥ ማደግ፣ የቅርብ ሰዎችን በሞት በማጣት ምክንያት የሚመጣ ውጥረት፣ ሀዘን /ብስጭት፣ መረበሽ ፍርሃት ፣ከልጅነት ጀምሮ የተለያዩ አካላዊ፣ ጾታዊ ወይም ስነ ልቦናዊ ጥቃቶች ዉስጥ ማለፍ፣ ወዘተ…
3. ማህበራዊ መንስኤዎች (social causes): ችግር፣ ስራ ማጣት፣ ስደት፣ ድህነት፣ ስራ አጥነት ፣ የእኔ የሚሉትና ችግራቸውን የሚያካፍሉት ሰው አለመኖር፣ መገለል፣ ብቸኝነት… ወዘተ
የአዕምሮ ህመም ባብዛኛዉ የሚከሰተዉ ግን ተጋላጭነታቸዉ ከፍ ያሉ ሰዎች ላይ ሌሎች የሚቀሰቅሱ ምክንያቶች ወይም ስነ ልቦናዊ ዉጥረቶች (Psychological Stressors) ሲፈጠሩ ነዉ።
እንደ አለም ጤና ጥበቃ ጥናት መሰረት ከ 5 ሰዉ አንዱ የአዕምሮ ህመም በህይወቱ ሊገጥመዉ እንደሚችል ያሳያል። በአለማችን በ 2030 እንደ አዉሮፓዉያወን አቆጣጠር በተራ ቁጥር አንድ ላይ የሚቀመጥ የጤና እክል ወይም ዲስኤቢሊቲ ምክንያት እንደሚሆን ያሳያል።
በሀገራችን የተሰሩ ጥናቶችም ቢያንስ እስከ 28% ድረስ የሚደርሱ የህብረተሰባችን ክፍሎች ለተለያዩ የአዕምሮ ህመሞች ተጋላጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያሳያል። አሁን ላይ በሀገራችን ላይ እየበዛ የመምጣቱ ምክንያቶች መካከል ሱሰኝነት ይካተትበታል። ለምሳሌ፡- በሀገራችን ጫት እስከ 64 በመቶ ድረስ የሚቃምበት አካባቢዎች ይገኛሉ። ወደ ሶስት በመቶ የሚያክሉ የህብረተሰባችን ክፍሎች ደግሞ በአስቸጋሪ የአልኮል አጠቃቀም ልማድ ዉስጥ ይገኛሉ። ማሪዋና እስከ 1.5 በመቶ ያክል ተጠቃሚ በሀገራችን ይገኛሉ፣ የማሪዋና ተጠቃሚዎች ግን እጅግ እየጨመረ ነዉ። ሱስ በራሱ ለ አዕምሮ ህመም ሊያጋልጥ ቢችልም በተዘዋዋሪ መንገድ ደግሞ የተለያዩ የጤና፣ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ስነልቦናዊ ጫና የተነሳ ለአዕምሮ ህመም ሊዳርግ ይችላል።
ከነዚህም በተጨማሪ ጉዳዩን የሚያባብሰዉ በቂ የሆነ የአዕመሮ ጤና ግንዛቤ ያለመኖር፣ የተሳሳተ አመለካከት በህብረተሰቡ መንሰራፋት፣ ተገቢ ትኩረት ያለመሰጠት እና በቂ የሆነ የአዕምሮ ህክምና አገልጋዮችም ሆነ አገልግሎቱ በሀገራችን ያለመኖሩ ብሎም ህብረተሰባችን እርዳታ በጊዜ ያለመፈለጉ ይካተቱበታል።
ዶር አሥራት ሐብተጊዮርጊስ የሥነ አዕምሮ ስፔሻሊስት ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ