መካንነት ወይንም “infertility” የሚባለው አንድ ሰው ብቻውን የሚያጋጥመው ሳይሆን ሁለት ሰዎች አሊያም ባል እና ሚስትን የሚጋጥም ችግር ነው።
ሁለት ጥንዶች የመካንነት ችግር አጋጥሟቸዋል የሚባለውም ለአንድ ዓመት የግብረ ሥጋ ግንኙነት በአግባቡ ወይንም በሳምንት ሦስት ቀንና ከዚያን በላይ ከፈጸሙና ምንም ዓይነት የወሊድ መቆጣጠሪያ መንገድ ሳይጠቀሙ መውለድ ካልቻሉ ነው።
በዓለም ላይ ስንቶች ለመካንነት ይጋለጣሉ፤ ምክንያቶቹ ምንድን ናቸው?
• በትዳር ጥምረት ፈጥረው እና የግብረ ስጋ ግንኙነት በአግባቡ ከሚፈፅሙ ሰዎች ውስጥ ከ80 እስከ 90 ከመቶ የሚሆኑት የመውለድ አሊያም ዘራቸውን የመተካት ዕድል አላቸው። ይሁንና በተለያዩ ምክንያቶች ቀሪዎቹ ለመካንነት ሊጋለጡ ይችላሉ። መካንነት በወንድ አሊያም ደግሞ በሴቷ መውለድ አለመቻል ሊከሰት ይችላል። አልፎ አልፎ ደግሞ ሁለቱም በተመሳሳይ ይህ ችግር ሊገጥማቸው ይችላል። በዚህም መሠረት 20 ከመቶ መካንነት በወንዶች፣ 38 ከመቶ በሴቶች እና 27 ከመቶ ደግሞ በወንዶችና ሴቶች ተመሳሳይ ችግር መካንነት እንደሚከሰት ይታወቃል። 15 ከመቶ የመካንነት ችግር ደግሞ በውል አይታወቅም። ችግሩን የሚታወቀውም በህክምና ተቋማት በሚደረግ ምርመራ ነው።
ሴቶችን ለመካንነት የሚጋልጡ ችግሮች ወይንም ህመሞች መካከል
– የእንቁላል መዛባት (Ovulatory disorders)
– የማህፀን ውስጥ ስሮች መበታተን (Endometriosis)
– የመራቢያ ክፍሎች መጠባበቅ አሊያም መያያዝ (Pelvic adhesions)
– የፕሮላክቲን ዕጢ መብዛት (Hyperprolactinemia)
– የዘር መተላለፊያ ቦይ መዘጋት (Tubal blockage)
– ሌሎች የዘር መተላለፊያ ቦይ ህመሞች (Other tubal abnormalities) ያካትታል።
ለወንዶች መካንነት የሚጋልጡ ችግሮች
– የፒቱታሪ ዕጢ በሽታ እና ሃይፕትሎማሲ (secondary hypogonadism)
– የወንድ ዘር መተላለፊያ ቦይ ህመም (sperm transport disorder)
– የመራቢያ ብልት ህመም (Testicular disease)
– ምክንያታቸው የማይታወቁ ሌሎች ችግሮች (Idiopathic) ናቸው።
መካንነት ሲከሰት ወደ ጤና ተቋማት መሄድ ያስፈልጋል?
ባልና ሚስት በአንድ ዓመት ውስጥ ተገቢውን የግብረ ስጋ ግንኙነት እየፈፀሙ እርግዝና ካልተፈጠረ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ መመርመር ይጠበቅባቸዋል። ሆኖም የሴቷ ዕድሜ ከ35 ዓመት በላይ ከሆነ አንድ ዓመት ሳይጠብቁ ከስድስት ወር በኋላ ሄደው መመርመር አለባቸው። ይህም ዕድሜ በጨመረ ቁጥር የማርገዝ ዕድል እየቀነሰ ስለመሄድና ጊዜ መውሰድ አስፈላጊ ባለመሆኑ በወቅቱ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል።
ለምርምራ ወደ ህክምና ተቋማት መሄድ ያለበት ወንዱ ወይስ ሴት?
እንደ ባህል ሆኖ በብዛት መሃን ሆነች የምትባለው ሴቷ ነች። አንዳንድ ሰዎችም አልፎ አልፎም ሚስቴ መሃን ሆናለች በሚል ትዳራቸውን ያፈርሳሉ። ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው መካንነት በወንድ፣ በሴት አሊያም ደግሞ የሁለቱም ችግር ሊሆን ይችላል። ታዲያ መካንነት የሴቷ ችግር ብቻ ነው ብሎ መውሰድ እጅግ የተሳሳተ አመለካከት ነው። ስለሆነም ሁለቱም በጋራ በጤና ተቋማት ሊመረመሩ ይገባል።
በህክምና ተቋማት ምን መፍትሄ ሊሰጥ ይችላል?
ለመካንነት መፍትሄ ለመስጠት በመጀመሪያ ደረጃ መካንነትን ያስከተለ ውን ችግር ምንድን ነው ብሎ ከመለየት ይጀምራል። ችግሩ በህክምና ከተለየ በኋም የተለያዩ ህክምናዎች ሊሰጡ ይችላሉ። ከእነዚህም ውስጥ በብዛት ከሚሰጡ ህክምናዎች መካከል የሚከተ ሉት ይጠቀሳሉ።
መውለድ ለማችይሉ ወንዶች፣ (assisted reproductive therapy) በተለያዩ ምክንያቶች በቂ የወንድ ዘር (ስፐርም) ለሌላቸው ወንዶች ወይንም አነስተኛ ዘር ያላቸው ወንዶች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ዘራቸውን በመውሰድ ወደ ሴቷ ማህፀን እንዲገባና ከሴቷ እንቁላል ጋር እንዲዋሃድ ብሎም እርግዝና እንዲፈጠር ማድረግ ይቻላል። እንደ ችግሮቹ ዓይነትም ሌሎች መፍትሄዎች ይኖራሉ።
መውለድ ለማይችሉ ሴቶች- ህመሞቹ፣ እንደሚለያዩ ሁሉ መፍትሄያቸውም የተለያየ ነው። ለአብነት የዘር መተላለፊያ ቦይ ከተዘጋ፣ የማህፀን ህመም አሊያም ደግሞ ሌሎች ኢንፌክሽኖች የተከሰቱ እንደሆነ በህክምና በመታገዝ እርግዝና እንዲፈጠር ማድረግ ይቻላል። የተለያዩ ሆርሞኖች መዛባትና የዘር እንቁላል ችግሮችንም በሃኪም የታዘዘ መድኃኒት በመውሰድ ማስተካከል ይቻላል።
ራስን በራስ ማገዝ ይቻል ይሆን?
ቢያንስ በሣምንት ሦስት ቀን የግብረ ሥጋ ግንኙነት ማድረግ ያስፈልጋል። ግንኙነት በሚደረግበት ወቅትም እርግዝና በከፍተኛ ደረጃ ሊፈጠር የሚችልባቸውን ቀናቶች መለየት አስፈላጊ ነው። ይህ ማለትም የወር አበባ ከመጣ (the start date) ከ9 እስከ 19ኛ ቀን ያሉትን ያካትታል።
– አዕምሮ የሚረብሹ ነገሮች የወር አበባ ዑደትንና የእንቁላል ወይንም የሴት የዘር ፍሬ ዝግጅትን ስለሚያሳንሱና ስለሚያዛቡ መሰል ችግሮችን ማቃለል አሊያም መራቅ ያስፈልጋል።
– ክብደት መቀነስ
– የኬሚካል ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚሠሩ ከሆነ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ
– ለሱስ የሚጋልጡ ዕጾችን አለመጠቀም፣ ከአልኮልና ትንባሆ መራቅና የተለያዩ ሱሶችን መቀነስና የመሳሰሉትን ያካትታል።