የአእምሮ ህመምን ማግለል

የታፋው አጥንት ተሰብሮ ወደ አንድ ሆስፒታል ያቀናል።

ከዛም ድንገተኛ ክፍል ውስጥ እንዲቆይ ይደረጋል። እሱ ግን እየጮኸ ይወራጫል። የህክምና ታሪኩን ሲጠይቁት የአእምሮ ህመም አለብኝ ብሎ እንደነበረ ትዝ አላቸው። ወደ አማኑኤል ሪፈር ፃፉለት።
.
አማኑኤል ከመጣ በኋላ አገኘሁትና አናገርኩት። በትክክል ይናገራል። የተሰበረው እግሩ ህመም ግን እየጠዘጠዘው ነው። የህመም ማስታገሻ በደንብ ሰጠነው። ጩኸቱ እየቀነሰ ሄደ።
.
የአጥንት ህክምና እንዲያገኝ መልሰን ልንልከው ስንል ግን ከቅበላ ባለሞያ (Liaison) ያገኘነው ምላሽ "እሱ ያስቸግራል። አንቀበልም! እዛው አማኑኤል ሆኖ ይታከም።" አለ። እየተናደድኩ ስመጣ ይታወቀኛል።
.
እራሴን አረጋግቼ "የህክምና ቅደም ተከተል ላይ ለህይወት አስጊ የሆኑ ነገሮች ከታከሙ በኋላ የሚመጡት የአካል ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ህመሞች ናቸው። የአእምሮ ጤንነቱን ጊዜ ሰጥቼ መርምሬዋለሁ፤ ከባድ የአእምሮ ህመም የለበትም። የታፋው አጥንት ግን ተሰብሯል። ደግሞ እኔም ሆንኩ አንተ የታፋችን አጥንት ቢሰበር እሪሪሪሪ ማለታችን ይቀራል እንዴ?" አልኩት።
.
ከሁለቱ ምክኒያቶች የትኛው እንዳሳመነው አላውቅም። ብቻ "እ...ሺ" አለ።
.
ከባድ የአእምሮ ህመም ያለባቸው ሰዎች አስር አመት ቀደም ብለው የሚሞቱበት ምክኒያት የአካል ህመም ሲያጋጥማቸው ወደ ህክምና ቶሎ ስለማይወሰዱ ፤ ከተወሰዱም በኋላ በተገቢው መንገድ ስለማይታከሙ ነው።
.
ያለ አእምሮ ጤና ፤ ጤና የለም!
ዶ/ር ዮናስ ላቀው